kaleXmat

Welcome to Kalexmat.com - Your #1 Source for Creative Arts and Designs.

ኢትዮጵያን ማብቃት

  • የሚከተለው ጽሁፍ ሌሎች ሰዎችጋም እንዲደርስ በጎ ተጽዕኖም ይኖረው ዘንድ share እና tag እናድርግ።እነሆ ደራሲ ወይም ጸሃፊ አይደለሁምና ከቃላት አሰካክ እና አጣጣሌ ይልቅ ሃሳቡ ላይ ታመዝኑልኝ ዘንድ እማጸናለው። እና ይህቺን አጭር ጽሁፍ ከጸሃፊው እውቅናና ፈቃድ ውጪ በከፊልም ይሁን በሙሉ በማንኛውም ዘመነኛ መልኩ ማባዛትም ሆነ ማሰራጨት መብታቹ ነው!…. መልካም ንባብ!

የ ኢትዮ ፊልሞች ብዙም አይመቹኝም! ከሌላው አለም አወዳድሬው ሳይሆን እንዲው ብሽቅ ብግን የሚያረጉ ብዙ ነገሮች ስለማይ ነው፤ በዚህም ምክንያት ኢትዮጲያ ውስጥ የሚሰሩ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን (ፊልሞች)ን ማየት ካቆምኩ ረዥም ግዜ ሆኖኛል፤ ይሁን እንጂ በአንድ አጋጣሚ ይሄን ‘ወደ ኋላ’ የተሰኘ ግሩም ፊልም ለማየት ቻልኩ፤ ፊልሙ መቼ ሲኒማ ላይ እንደዋለ ምንም የማውቀው ታሪክ የለም በቃ አየውት ወደድኩት! እና ሌላ የማላውቀው ነገር ቢኖር ከዚ በኋላ ስንት ግዜ እየደጋገምኩ እንደማየው ነው ። ለእኔ አንድ ፊልም ጥሩ ፊልም ለመባል እያዝናና የሚያስተምር፣ የ ገጸ-ባህርያቶቹ ስሜት እንዲሁም የፊልሙ እሳቤ ወደ ተደራሲያኑ መተላለፍ ሲችል፣ ድምጽ እና መብራት አጠቃቀም፣ የ ገጸ-ባህርያት መረጣ እና ችሎታ እንዲሁም በዋናነት ፊልሙ በ ማህበረሰቡ ላይ የሚፈጥረው የበጎ ተጽዕኖ መጠን የሚሉት ጥቂት መስፈርቶቼ ናቸው። ፊልሙ ፍጹም ኢትዮጵያዊነታችንን ፍንትው አርጎ ያሳየ፤ ጀግንነታችን በጦርሜዳ ላይ ብቻ እንዳልነበረ ይልቁንም በዕደ ጥበብ፣ በስነ ህክምና፣ በስነ ሰዕል፣ በስነ ፈለክ፣ በኪነ ህንጻ፣ በስነ ህግ፣ በስነ ጽሁፍ፣ በስነ ታሪክ፣ በስነ ምርምር(ስነ መንፈስ) በመሳሰሉት የአእምሮ ግኝቶች ላይም እንደነበር ያሳያል ለዚህም የ’ፊልሙ አዘጋጅ እና ደራሲ ማህሙድ ዳውድ’ እንዲሁም ‘ቀይ ቀበሮ ምስሎች’ ምስጋና ይገባቸዋል ባይ ነኝ።

ወደ ቁምነገሩ ስመለስ ኢትዮጵያ ሃገራችንን ወደ ቀድሞ ታሪኳ እና ወደ ሃያልነቷ ለመመለስ ማንንም ሳንፈልግ የማንም እርዳታ እና ገንዘብ ሳያስፈልገን እኔ እና እናንተ ብቻ በመሆን ለምን ታሪክ አንሰራም?…እ? ምናልባት እንዴት ወዴት ምናምን የሚሉ ጥያቄዎችን ልትጥይቁ ትችላላቹ። ለነዚ ሁሉ ከባድ መሳይ ጥያቄዎቻቹ ግን የምሰጣቹ ማለፊያ መልስ ቢኖር…”ራሳችንን በማክሰም” የሚለው ነው።አዎ ይሄ ማለት ከራሳችን በላይ ለተከታይ ትውልድ ለመጪው ግዜ ተረካቢ ማሰብ ማለት ነው። ወንድም እህቶቼ አንድ መስማት ማትፈልጉት ግን ደሞ እውነት የሆነ ነገር ልንገራቹ በእኛ የህይወት ዘመን የግል ኑሯችሁን ታሻሽሉ ይሆናል እንጂ ኢትዮጲያችን በጭራሽ ካደጉ ሀገራት ተርታ ልትሰለፍም ሆነ ልትመደብ አትችልም! ቁርጣችሁን እወቁት እንግዲ።ከኛ በታች ያሉትም የኛን ፈለግ ነውና ሚከተሉት ልክ እንደኛ ለራሳቸው ኖረው ለራሳቸው ይሞታሉ ግብአተ መሬታቸውም ይከናወናል ህይወትም ይቀጥላል ሀገራችንም መንፏቀቋን ትቀጥላለች።እኛ አራዳ ትውልዶችም አይደለን? ይሄ እንዲፈጠር ከቶ አንፈቅድም! እስኪ አስቡት ያኔ ስልጣኔያችን ጫፍ በደረሰበት ዘመን፣ ኢትዮጵያያያ… ሲባል መላው አለም በሚርበደበድበት ግዜ ይሮሩ የነበሩትን ዘመዶቻችንን! ምን ጭንቀት ምንስ ችግር ነበር? ሳስበው ግን እነዛ የጥንት ዘመዶቻችን ፤ አያት አባቶቻቸው እንዴት አድርገው ለዛ ክብር እንዳበቋቸው የተረዱ አይመስለኝም ቢሆንማ ኖሮ ከጀብዳችን ታሪክ እኩል ጥበብን፣ፈጠራን እንዲሁም ምርምር አደራረግ መንገዱን በቀሰሙ ነበር ቀስመውም ለልጅ ልጆቻችው ማስተላለፍ በቻሉ ነበር እኛም ይሄን ግዜ በፖለቲካው፣ በኢኮኖሚው እንዲሁም በተለያዩ ዘርፎች ግንባር ቀደም ሆንን በመራን ነበር። አሁን እየሄድን ባለንበት አካሄድ ጥቂት ለውጥ ወይም ከሌላው አለም አንጻራዊ የፍጥነት እርምጃ ላይ ልንደርስ እንችል ይሆናል ለመድረስ በምናረገው ፍጭርጭሪት ግን የሆነ ቦታ ላይ መዳከም ከመጣ ከበፊቱ በላይ ርቀታችን ይሰፋል ስለዚ ራሳችንን በማክሰምና በቀጣዩ ትውልድ ላይ አቅምን አሰባስቦ ወይ በመሮጥ ወይ ረጅም መሳይ አቋራጭ መንገድ በመጠቀም ልንደርስባቸው ይገባል።

ራሳችንን እናክስም! አሁን ካለንበት ዘመናዊ ባርነት እኛ መውጣት ባንችልም ቀጣይ ትውልዶቻችን ግን ነጻ እንዲወጡ ማድረግ እንችላለን። ያደገ ሀገር ያደገ ኑሮ ብልጭልጩ ሁሉ ያጓጓን ይሆናል! እነሆ ሰው ነንና ልንጓጓም ይገባል። እላፊ መፈለጋችን ግን ባርያቸው ቢያደርገን እንጂ ክብራችንን አይመልስልንም ከዛ ይልቅ አብዝቶ ለሚፈልገን እላፊ ለሚጓጓልን ህዝብ፡ ሰው እንሁንለት …ንጉስም ያደርገናል ከዙፋኑ ማማም ያስቀምጠናል።አሁን ላይ አብዛኞቻችን የተማርን የተመራመርን የምንባል እኛ እውነት ምንድነው የተማርነው ምንስ ነው የተመራመርነው? እሺ ምርምራችን ለወረቀት ነበር ወይስ የእውነት የሃገራችንን ቁልፍ ችግር መፍታት የሚያስችል ሲያንገበግበን የነበረ ነገር ነው?… እኔ በመሰረቱ የንድፍ ባለሙያ (Designer)ነኝ እስካሁን ግን ኪሴን ሚያሳድግልኝ ነገር እንጂ የሃገሬን ክብር ሊያስጠብቅ ፣ የሃገሬን ሰው ሊያነቃቃ የሚችል፣ የሃገሬን ዘርፈ ብዙ ጥበባቶች እኔ በተሰማራውበት ዘርፍ በበቂ ሁኔታ ሊያሳድግ የሚችል ስራን ሰርቼያልው ብዬ ስለማላስብ ጸጸት ይሰማኛል። ደግሞም መምህር ነኝ ያውም ብዙ ትውልድ ለመቅረጽ የሚያስችል ቁልፍ ቦታ ላይ የምገኝ በአስተምሮቴ ካሪኩለሙ ሚያዘውን ሞጁሉ ሚለውን ብቻ ሳይሆን ተማሪ ትክክለኛ ማንነቱን ፈልጎ ሚያገኝበትን መንገድ እና እድሉን ሚፈጥርበትን ስርአት ለመቅረጽ የምጥር! ይሁን እንጂ ጥረቴ በቂ እንዳልሆነ ይሰማኛል እና በዚህም ተጨማሪ ጸጸት ይሰማኛል። ልብስ ሰፊ፣ ሃኪም ዶክተር፣ ሾፈር፣ አናጺ፣ አርቲስት( All artists and designers, decorative and fine artists, etc), ዳኛ ወዘተ… ሙያ ውስጥ ያለን ምን ያህል ኢትዮጲያ ላይ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል ስራን ለመስራት አስበን እናውቃለን ሃሳቡስ ምን ያህል ማህበረሰብ ላይ በጎ ተጽዕኖ ነበረው? ይሄን ሃሳባችንንስ እንዳናሳካው ምንድን ነበር የያዘን? አዎ እነዚህ ሁሉ ሃሳቦች በጋራ ሲሆኑ በጣም ቀለል ይላሉ እንዲሁም ይበልጥ ሊዳብሩ እና ወደመሬትም በቀላሉ ሊወርዱ ይችላሉ። አንተ የጎደለህን ሃሳብ እሷ ትሞላዋለች፣ እሷ የተቸገረችበትን እቅድ አንተ ታረቅላታለህ፣ የኔን የመፍትሄ ሃሳብ ታሻሽልልኝኛለህ አንቺም ትገመግሚልኛለሽ፤ እኛው ከስመን፣እኛው ለኛዪቱ ምስኪኒቱ ድሃይቱ ሃገራችን መድሃኒት፣ ለእድገቷም ምክንያት መሆን እንችላለን። ቸር ያቆየን!
ቃለአብ ማቲዎስ kalex mat
ታህሳስ 26 2012.

Discover more from kaleXmat

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading

Scroll to Top